God is right

Rahel Fekadu Terefe

What did God do? What is He doing now?

By God's grace I will bring you real life testimonies. Hearing, seeing, reading the works of God will uplift ur spirit. COMING UP...

                                            ም ስ ክ ር ነ ት

ቀጥሎ ያለውን ምስክርነት ያገኘሁት ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ጌሴም የሚባል የክርስቲያን መፅሄት ላይ ነው። መፅሄቱ አሁንም በገቢያ ላይ አለ። ምስክርነቱን በሁለት ክፍል የማቀርበው ሲሆን ማናቸውም ጥያቄ ወይንም አስተያየት መጨረሻ ላይ በምለጥፈው አድራሻ መሰረት ማቅረብ ትችላላችሁ። ያለአንዳች እርማት ምስክርነቱ እነሆ…

 

                                    ክፍል አንድ     

 ልጅነትን ሳላውቀው አደግሁ፡-

ሰው በዘመኑ የሚያልፍበት ጎዳና የተለያየና ውስብስብ ነው ለአንዱ ሁሉ ቀላል ሲሆን ሌላው ወደር የሌለው መከራ ውስጥ ይጓዛል። ሁሉን አስችሎ የሚያሳልፍ ግን እግዚአብሄር በዙፋኑ ላይ አለ። ይህንን ያልነው ከእናቷ ማህፀን ጀምሮ የስቃይ ሰለባ ስለነበረችውና ለእርሷ የተገለጠውን የእግዚአብር የማዳን እጅ መናገር ወደን ነው። ቤተልሄም አበበ ቀይ መልከ መልካም ወጣት ነች። ኮልፌ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን የሚገለጠውን የእግዚአብሔርን ጣት ለማየት በሄድንበት ጊዜ ነበር ያገኘናት። የእግዚአብሄር ሰው መጋቢ መስፍን ሙሉጌታ በአስምና ጨጓራ ህመም ለሚሰቃዩ ሰዎቸ ለመፀለይ ደረክ ጠቷቸው ከተደረደሩት ሰዎች መካከል የሁላችንን ስሜት የሳበው ከአይኗ አልፎ አንገቷ ድረስ የሚወርደው የቤተልሄም እንባ … ነበር። የደስታ እንባ… ከውስጥ …ከልብ ፍንቅል ብሎ የወጣ መሆኑ ያሳብቃል… በእውነት የእግዚአብሄር ጣት እንደነካት ከፊቷ ላይ የሚነበበው ስሜት ፍንትው አድርጎ ያሳያል።

 ምን ሆና ይሆን? የሚል ጥያቄ በሚያይዋት ሁሉ ልብ እንዳለ እርግጥ ነው። ድንገት ፓስተሩ "ልጄ ጌታ ምን አደረገልሽ?" አላት። እየተንሰቀሰቀች መናገር ጀመረች። ጉባኤው በእልልታና በጭብጨባ አጀባት። ስለሆነላት የብዙዎች ዓይን በእንባ ረጠበ። ይህንኑ ፎቶግራፍ አንስተን ባለፈው እትማችን የፊት ገፅ ላይ ከመጋቢ መስፍን ጋር አውጥተን ነበር። ዛሬ ሙሉ አስደናቂ ምስክርቷን ይዘን አሁን መጥተናል።ተከታተሉት።

 "ቤተልሄም አበበ እባላለሁ። 1979 ዓ.ም ደብረዘይት ከተማ ተወለድኩ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ቤተልሄም በሚባል የሚሽኖች ትምህርት ቤት መማር ጀምሬ ቤተሰቦቼ ትምህርት ቤቱ የክርስቲያኖች መሆኑን ሲሰሙ በአስቸኳይ ከዚያ አስወጥተውኝ ህብረት የሚባል የመንግስት ትምህርት ቤት እንድገባ ተደረግሁ። ምክንያቱም ቤታችን አጋንንት አምላክ ተደርጎ ይመለክ ስለነበር ነው።" ብላ ትክዝ አላት። ያለፈ አስከፊው የሂወት ውጣ ውረዷ ትዝ አላት። መራራና ዘግናኝ ቀኖቿ በፊቷ ተደረደሩ። ዛሬ  ላይ በድል አድራጊው ጌታ የተዋረደውን የዲያቢሎስ ስራ የጨለማውን ስራ ግለጡት እንዲል ልታጋልጠው ትተርክልን ጀመር። "ከውልደቴም እኔ እንድወለድ አልተፈለገም ነበር። እናቴ ስትነግረኝ እንደተረገዝኩ ሀብሏን ሽጣ እኔን ለማስወረድ መድሀኒት ወስዳ አልተሳካላትምና ፅንሱ አድጎ በመወለጃዬ ጊዜ በአዋላጆች ምክንያት ብዙ ደም ስለፈሰሳት እናቴ ወዲያው ወደ ሆስፒታል ሄዳ በብዙ ጭንቅ እንደተወለድኩ አጫውታኛለች።

 ከተወለድኩ ኋላ አባቴ "ስወስን" የሚል ስም አወጣልኝ። በወቅቱ አባቴ ለምን ይህን ስም እንዳወጣልኝ፤ ምን እንደተወሰነ አላውቅም። ነገር ግን የመንፈስ አሰራር እንዳለበት አስባለሁ። የአባቴ ቤተሰቦቹ ያወጡለት ስም አበበ ሲሆን መንፈሱ የሚጠራው "ወሎ በላ" ብሎ ነው። ያ ከልጅነቱ ጀምሮ እራሱን የቻለ ታሪክ ለው። እናቴ ግን ስሜ በጣም ስላስጠላት አንዴ ማህሌት አንዴ ኢየሩሳሌም ቢሉኝም ሊዋጥላት አልቻለም። እቤታችን በፍፁም መፅሐፍ ቅዱስ ማንበብ አይቻልም። አንድ ቀን ግን በሚገርም ሁኔታ መፅሐፍ ቅዱስ ስታነብ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን ከተማ አገኘችና ያንን ስም ስለወደደችው "ቤተልሄም" የሚል ስም እንዳወጣችልኝ ነግራኛለች። አባቴ በወቅቱ ባይቃወምም እያደኩ ስመጣ ግን ለእኔ ያለው ጥላቻ ይሄ ነው የሚባል አልነበረም። ሰበብ እየፈለገ በጭካኔ ይደበድበኝ እጅግም ያሰቃየኝ ነበር የኔ ስቃይ ለጎረቤቶቼ ሁሉ ስቃይ እስኪሆን መራራ ነበር። "አንቺ የእናትሽ ልጅ አባትሽን ፈልጊ እኔ አባትሽ አይደለሁም" ይላል። ቡና አፍልቼለት የተለያየ  ነገር አድርጌ ላስደስተው እሞክራለሁ። ግን እንደሌሎች እህቶቼና ውንድሞቼ በጥሩ ፊት አይቀበለኝም።

 በቤታችን ውስጥ የሚመለኩት አጋንንቶች የየራሳቸው ቀኖች አሏቸው። ረቡዕ ሐሙስ ማክሰኞ እና እሁድ የተለዩ ቀኖች ናቸው። በተለይ ረቡዕ "ሼህ አንበሶ" የሚባል መንፈስ ይመለካል። ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ አዳልሞቴ፣ ወሰንጋላ፣ ብር አለጋ የሚባሉ መናፍስቶች በቤታችን ይመለኩ ነበር። ለእነሱ ብቻ የተለየ ቤት ነበራቸው። አባቴ እዚያ ውስጥ ሆኖ ነበር የሚያመልከውና ቡና የሚያፈላው። እዚያ ቤት የሚገባው ሰው መንፈሱ የወደደው በተለይ ልጃገረድ ወይም ያላገባች ሴት መሆን አለባት። ከልጅነቴ ጀምሮ የማየው ነገር ቤታችን ውስጥ ማንም ዝም ብሎ አይደለም የሚገባው የሚደረገው ነገር ሁሉ ምክንያት አለው። የተለያዩ ስርዓቶች አሉ። ለምሳሌ አባቴ የተለያዩ ቅጠሎች ሰንሰል፣ የምድር እንቧይ፣ ግራዋ የሚባሉ ሌሎችም ስማቸውን የማላውቃቸው ቀጠላ ቅጠሎች አንድ ላይ ተጨፍጭፈው በእሱ እግራችንን ተለቃልቀን ነው የምንገባው። አባቴ ግን ገላውን ታጥቦበት ነው የሚገባው።

 ሌላው ሴት ልጅ የወር አበባ ላይ ከሆነች ቡና የሚያፈላው ሰው በር ላይ ሆኖ ሲኒ ለሲኒ ሳይነካካ በሌላ እቃ ተገልብጦላት ነው የሚጠጣው እንጂ እቤት ውስጥ እናቴም እንኳን አትገባም። እንዲሁም አንዳንድ ሰዎች ከምንጃር፣ ከጎጃም፣ ከአዲስ አበባ ብዙ ሰዎች በዝምድና መልክ የሚመጡ ነበሩ። በኋላ ስረዳ ከመንፈሱ ጋር ያላቸው ትስር ነው እንጂ ምንም ዝምድና የለንም። መፍትሄ ፍለጋ ብለው ብዙ ሰዎች ይመጡ ነበር። በሌላ አነጋገር አባቴ ጥንቆላ ስራ ተሰማርቶ ነበር ማለት ነው። እኔ ገና ከብላቴንነቴ ጀምሮ ለመንፈሱ የተሰጠሁ ብሆንም በውስጤ የምረዳውን ነገር የመናገር አቅም አልነበረኝም። አባቴ ደግሞ ለምን እንደሆነ አላውቅም እጅግ ይጠላኝ ነበር" ብላ ፀጥ አለች። በመካከላችን ጥቂት ዝምታ ሆነ። ደረሰባትን በደል እያስታወሰች እንባ በአይኖቿ  ግጥም አለ። እልህ እየተናነቃት እንደምንም ትንፍስ አለች።

 "አንድ ቀን ሊያስገርፈኝ የሚችል አንዳች ጥፋት አልነበረም በአባቴ ውስጥ ያለው መንፈስ ደሜን ፈልጎ አባቴን አስነሳው። በፍርድ ቤት ሊያስፈርድበት የሚችል የድብደባ ወንጀል ፈፀመብኝ። ጠዋት ሁለት ሰዓት መግረፍ የጀመረ ስምንት ሰዓት ነበር ያቆመው። ያለማቋረጥ ለስድስት ሰዓት መግረፍ የጀመረ ለስድስት ሰዓት ያህል ደበደበኝ። ብዙ ደም ስለፈሰሰኝ ልብሴ በደሜ ርሶ ከሰውነቴ ጋር ተጣበቀ። ብዙ ሰዎች እናቴን ለምን አትከሽውም ሲሏት እሷ ግን "ለአንድ ለመድሀኒያለም ሰጥቻለሁ" ነበር የምትለው። በአባቴ ምክንያት እናቴ ብዙ ተጎድታለች። ለስሙ ሚስቱ ትባል እንጂ እሱ ያለገደብ ከብዙ ሴቶች የሚሴስንና ለእናቴ አክብሮት ያልነበረው ሰው ነበር። የቤታችን የመጀመሪያ ልጅ ስለሆንኩ ከታናሽነቴ ጀምሮ የስራ ጫና እኔ ላይ ስለሆነ በጣም እጎዳ ነበር። መካደም አለ፣ ቡና ማፍላት፣ ሌላው ቀርቶ የቤቱ ስርዓት ብቻ አስመርሮ ከቤት የሚያስወጣ ነው። ስንቀመጥ እግራችንን አቆላልፈን ነበር የምንቀመጠው። በዚያ ውስጥ ሁሉ እግዚአብሔር ለራሱ ዓላማ ስለፈለገኝ ትዕግስትን ሰጥቶ በሕይወት አኖረኝ። ቤታችን ውስጥ የሚደረገውን አምልኮ ለመግለፅ የሚከብድ ነበር። አንዳንዴ አባቴ እያመለከ መልኩ ይለዋወጥ ነበር። ጫት መቃም ይተውና ግራዋ ይቅማል። በዚህ እኛ በጣም ነበር የምንቸገረው። ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንን ያስቆረቆረ ነው። ሌሊት ሄዶ ደውል የሚያስደውለው እሱ ነው። ብዙ ቄሶች እኛ ቤት ይመጣሉ። ተጋብዛው ዳዊት ደግመው ነው የሚሄዱትና "እንደአባትሽ አይነት ጥሩ ሰው የለም" ይሉኛል። በመጥፎ ድርጊቱ ማውቀውን አባቴን መልዓክ ሊያደርጉልኝ ይጥራሉ። እኔም በሀይማኖተኝነት የምታማ አልነበርኩም። እህል ሳልቀምስ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ቆሜ የማስቀድስ ነበርኩ።  ቤተክርስቲያን ስንሄድ በስመ አብ ወልድ እንልና ስንመለስ ደግሞ "አሻዱ አላህ" ነው የምንለው። አባቴም "አዩ ሞሚና እናታችን" እያለ የአርሲዋ እመቤት የሚላትን አጋንንት ሲለማመን ያድራል። መንፈሱ ሲወርድ በአባታችን ላይ ሆኖ ከሳቀ ነገር አለ ማለት ነው።

ከሳቀ ሰው ሊሞት ይችላል። እንደውም በዚያን ሰዓት ቢመርቅ ጥሩ ነው ይባላል። እኛ ቤት የተለያዩ መድሀኒቶች ይቀመሙ ነበር። ለምሳሌ ስራይ /ሰው መድሀኒት ሲያደርጉባቸው መፍትሄ ብለው ሃውዛ የሚባል ጫት ይቀቀልና ውሃው አድሮ ለዚያ ሰው ተሰጥቶት ከጠጣው በኋላ ከውስጡ ትላትል ይወጣል መንፈሱ ይህንን ያደርግ ነበር። ሌላው እጅን የመጫን ፕሮግራም አለ ይህ ማለት ጭፍራውን አስወጥቶ አለቃውን ማስገባት ነው።

 እኔ እያደኩኝ ስመጣ "ፊት እንዳታስመቺ" ስለምባል ሰው ቀና ብዬ አላይም ነበር። አባታችንን እንኳ ሙሉ ለሙሉ አናየውም። አንደኛ ቁጣው ያስበረግገናል፣ ሌላው ያስፈራል ልናየው አንችልም። ከደብረዘይት ከመውጣታችን በፊት ስምንተኛ ክፍል እስክደርስ ድረስ ሰውን ቀና ብዬ አላይም። በዚህ ምክንያት ብዙ ጊዜ ከስልክ እንጨት ጋር እጋጫለሁ። ብዙ ወንዶች ይቀርቡኛል ግን በቀረቡኝ ቅፅበት ይለዩኛል። ይህ የመንፈሱ አሰራር ነው። ከመዋዕለ ህፃናት ጀምሮ እስከ አስረኛ ክፍል እስክደርስ ድረስ ጓደኛ አልነበረኝም። አንባቢው የልጅነት ጊዜዬን በእንዴት አይነት ብቸኝነት እንዳሳለፍኩ ሊገምት ይችላል። በእንዲህ አይነት ሁኔታ ለብዙ ዓመት ቆየሁ። አባቴንም በታማኝነት ነበር የማገለግለው። አንድም ቀን የሚያስገርም ነገር ኖሮኝ ባያውቅም እርግማንና ዱላ ተይተውኝ አያውቁም። እናትና አባታችን አንድ ግቢ ውስጥ ቢኖሩም ተለያይተው ስለነበር አንድ ግቢ ሆነን እናታችን ክፍል የምንሄደው እሁድ እሁድ ብቻ ስለነበር ስለምንናፍቅ ድንገት እናመሻለን።

 አንድ ቀን እናታችን ጋር አምሽተን በአጋጣሚ እሱ መጣና ግቡ አለን። እናቴን በጣም ስለምወዳትና በተጨማሪም እሱ ስላስመረረኝ "ለምን ግቡ ትለናለህ?" ስለው በጣም ተናደደ። ድንጋይ እየወረወረ አባረረኝ። ግቢያችን ሰፊ ነው ያንን ግቢ ዙሪያውን ሁሉ ነው ያስሮጠን። በኋላ ግን ያዘኝና እቤት አስገብቶኝ በአሰቃቂ ሁኔታ ገረፈ። ሰውነቴ ሁሉ አብ ስለነበር መነቀሳቀስ አልቻልኩም። በፍልጥ ነበር የመታኝ ሌላው በጣም ሀይለኛ አለንጋ ነበረው። እንደዚህ አይነት አለንጋ እስካሁን ድረስ አላየሁም። ሳስበው ከመንፈሱ ጋር ውርርስ ነበረው። ብዙ ጊዜ በሱ ሲገርፈኝ ሞተች ተብሎ ሆስፒታል እስኪወስዱኝ እደርስ ነበር ግን እዚያ ስደርስ ደህና ሆኜ እገኛለሁ። በዚህ ምክንያት ዶክተሮቹ ይቆጡ ነበር። አንገቴ ላይ ክታብ ነበር። እንዲሁም ከጦጣ ቆዳ የተሰራ ወገቤ ላይ የታሰረ ነበር። ያእኔ እንድድን ሳይሆን እስከመጨረሻው ልጅ እንዳልወልድ የተደረገ ነገር ነበር። ከተለያየ ቦታ  እኛ ቤት ሰዎች ሲመጡ ለአባቴ አንዳንዶቹ ብር ሌሎቹ በግ እንዲሁም ኩንታል ጤፍ ይዘው ሲመጡ ይቀበላቸው ነበር። መንፈሱ ግን በነፃ አገልግል ነበር የሚለው። በዚህ ምክንያት ከመንፈሱ ጋር ይጣሉ እንደነበር አስታውሳለሁ። ከዚያ ኋላ አባቴ ለአራት ዓመት በሳንባ ህመም ታመመ። ታሞ የሚደረገው ነገር አይቀርም። አሞሀል ብሎ መንፈሱ አያዝንለትም። አንዳንድ ጊዜ ሀሙስ ቆሞ ውሎ አድሮ ቅዳሜ የሚቀመጥበት፣ ጊዜ አለ። ይቅማል፣ ጀለቢያ ይለብሳል፣ መቁጠሪያ አለው ይቆጥራል ቡና የሚፈላው አርባ ሲኒ በሚይዝ ትልቅ ረከቦት ነው።  እዚህ ሲቅም "አቦል ጀባ ቃ ጀባ" እየተባለ ለመንፈሱ እተሰገደ ነው የሚመለከው አንዳንድ ጊዜ እፈታተነዋለሁ። ግቢያችን ውስጥ ሁለት ውሾች አሉና አባቴ በቂቤ የታሸ በሶ ይሰጠኝና ለውቹ እጆቼን አጠላልፌ እንድሰጥ ሲያዘኝ እሺ ብዬ በልቼው ነው የምገባው። ለመንፈሱ የሚሰራው ስራ በጣም አድካሚ ነው። ኑግ ዘይቱ እስኪወጣ ይወቀጣል። አስር ዓይነት ቆሎ ይዘጋጃል መስዋዕት ይደረጋል። እንዲሁም ጥፍጥሬ ተጫጭሶ ነው የሚገባው። ያ ካልተጨሰ ግቢያችን ውስጥ ያሉት እባቦች ያፏጫሉ። በነገራችን ላይ እባቦች በግቢያችን ይኖራሉ። አባቴም ከእነሱ ጋር ያወራ ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን ከአባቴ ጋር እየተጣላን እየተካረርን መጣን።

 አንድ ጊዜ እናቴ እህቷ ጋር ሄዳ መኖር ጀመረች። እዚያ የአክስቴ ልጅ አስም ነበረበትና ጴንጤዎች ጋር ሄዶ ይፈወስ ተብሎ ቤተክርስቲያን ወሰዱት። እሱ ከአስሙ ባይፈወስም የሀጢያት ፈውሱን የዘላለሙን ሕይወት ጌታ አግኝቶ እዛው ቀርቶ ማገልገል ጀምሯል። /ፈውሱን ግን ከብዙ ጊዜ በኋላ ተቀብሏል/ እኔ እዚያ በሄድኩበት ጊዜ እሱ የሚበላበት እቃ ሁሉ ተለይቶ ለብቻው እንደ እርኩስ ተቆጥሮ ነበር የሚኖረው። እኔ ከልጆች ጋር ልጫወት ስል አልጫወትም ስላሉኝ እሱ ቤት በር አካባቢ ስቀመጥ መዝሙር ሲዘምር ሰማሁት። መዝሙሩን አሁን ባላስተውሰውም "ኢየሱስ...ኢየሱስ" የሚለውን ቃል ግን ስሰማ ድንገት ሳላስበው ውስጤ የሆነ ነገር እየተፈጠረ መጣ። ትምህርት ቤት ስሄድ ከልጆች ጋር እደባደባለሁ ድንገት ሳያስቡት ነው በጥፊ የማጮላቸው። በትምህርቴ ፈዛዛ ከሚባሉት ልጆች መካከል ነው የምመደበው። ብዙ ጊዜ ትምህርቴን እየተከታተልኩ እያለ ለሌሎች ተማሪዎች አይታያቸውም ለእኔ ግን መንፈሱ በአካል ተገልጦ ይታየኛል። አስተማሪ እያስተማረ ቄስ የሚመስል ሰውዬ ድንገት ይገባና ሶስት ጊዜ ዴስኩን ይደበድባል። አስተማሪዬ "አሁን ምንድን ነው ያልኩት?" ሲለኝ እደነባበራለሁ። በዚህ ምክንያት ትምህርቴን መከታተል አልቻልኩም። በኋላ ወደ ደብረዘይት አባቴ ጋር ከተመለስኩ ኋላ አለመግባባታችን አለመግባባታችን እየከረረ ሄደ። ታናሽ እህቴ ግን ምንም የማትፈራና ለመንፈሱ የተዘጋጀውን ቆሎም ይሁን ሌላ ነገር ብልብሷ ዝግን አድርጋ ሮጣ የምትበላ ሆና ምንም አትሆንም ነበር። እኔ ግን ፈሪ ነኝ ምናልባት ደፍሬ እንኳን ከበላሁ ወዲያው ያስመልሰኛል።

 ታናናሾቼን የምሰበስብ አኔነኝና የሚያስፈልጉኝን ነገሮች ለመጠየቅ ወደእሱ ጋር ሄጄ "ደህና አደርክ?" ስለው "እንዴት እንዲህ ትይኛለሽ?" ብሎ ይደበድበኛል። በእንዲህ አይነት ሂይወት አብረን እያኖር እያለ አንድ ቀን ጠራኝና "ለምንድን ነው የምትረብሺኝን ሁሌ እንድመታሽ የምታደርጊኝ?" ሲለኝ "በቃ አንተ አባቴ አይደለህም" አልኩት። እህቴ ሁኔታችንን አይታ በቃ ዛሬ ሬሳዋ ወጣ ብላ ደንግጣለች። በኋላ ብሱ ስከራከር ጫማውን አንስቶ ሲወረውርብኝ ከእኔ አልፎ እሷን መታት። ብዙ ጊዜ የተለያዩ ነገሮች አንስቶ ይወረውርብኛል ግን ይስታል ልክ ሳጾል ዳዊትን ባሳደደ ጊዜ ጦሩን ሲወረውር ግድግዳ ላይ ይሰካ እንደነበር። ቡና አፍልቼለት ስካድመው ደግሞ እንደኔ ተጠርቶ ጫት የሚተፋበት ሰው የለም። የአባቴ እናት አያቴ ሲመርቁኝ "የማትቆረጠም የብረት መሶሶ ያድርግሽ" ይሉኝ ነበር። በወቅቱ ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም ሰው ሲሞት ለአባቴ እከሌ እኮ ሞተ ሲሉት "ተይው ባክሽ አራት እግሩን ይብላ" ይላል። እከሌን ወጋሁት ካለ ያ ሰው ይሞታል። ሌላው ሌሊት ላይ ጉጉት ሶስት ጊዜ ከጮኸች ሰው እንደሚሞት ያውቃል። እንደገና አንዳንድ ጊዜ ውሾች ለየት ባለ ድምፅ ይጮሀሉ። እነሱ ሲጮሁ ሰው እንደሚሞት ያውቃል። ያለንበት ቤት የተመሰረተው ብዙ ሰው የሞተበትና የሰው አጥንት ያለበት ነው። እንደውም አንድ ጊዜ ለእናቴ ሲፀለይላት በቤት ውስጥ  ረዥም የሰው ፀጉርና አውራጣት እንደተቀበረ ነው የተነገራት። እኛ ግቢ ፀጥታ የለበትም ምንም ሰው ሳይኖር የሚያቃጭል ደወልና የማያቋርጥ የተረባበሸ ድምፅ ይሰማል። ሌላው ግቢያችን ውስጥ ረጃጅም ሳር አለ። ዓመት በዓሎችን በመጡ ቁጥር ከሚመለክበት ቤት ጀምሮ ው ድረስ ነው የሚጎዘጎዘው። እንደገናም የሚርከፈከፍ ነገር አለ ግራና ቀኝ ይርከፈከፋል። በተለይ መስከረም ሲጠባ ልክ ከእንቅልፋችን እንደተነሳን ፌጦ ተወቅጦ በእንጀራ ተለውሶ ይመጣና አያታችን ያጎርሱናል። ቂቤ ይቀቡናል እንዲሁም አቴቴ ይደረጋል። እቤት ውስጥ እንጀራ ይጋገራል ድስት ሙሉ ወጥ ይሰራል። በነጋታው ሲታይ ባዶ ይሆናል።

...ይቀጥላል

 

                     ክፍል ሁለት

ልጅነትን ሳላውቀው አደግሁ፡-

ቀጣዩ ክፍል  

አንድ ቀን ማይረሳኝ ጊዜው በዓል ነው ሶስት አይነት ወጥ ተሰርቶ ለመጨለፍ ድስቱ ሲከፈት ጉንዳን ሞልቶበታል። መንፈሱ እንዲህ ያደርግ ነበር። የእኔና የአባቴ ፀብ የመጨረሻ በደረሰበትና ሊሞት አንድ ወር ሲቀረው ተረጋግምን " አንቺ በዚህ ወር ውስጥ ታመሽ አልጋ ላይ ተወድቂያለሽ" ሲለኝ " አንተ ነህ ታመህ አልጋ ላይ የምትወድቀው" አልኩት። እንዳልኩት አልቀረም ታመመና ሆስፒታል ገባ እኔ ነበርኩ የማሰታምመውና መጨረሻ ላይ በሽታው በጣም ስለፀናበት ሀኪሞች አይድንም ብለው ስለመለሱት እቤት ተኛ። ለነገሩ መንፈሱም እየፎከረ ነበር እንደሚገድለው። አባቴ ግንቦት ወርን በጣም ይፈራ ነበር እኛ ግቢ ሁልጊዜ ግንቦት ወር ላይ በትልቅ ድስት ንፍሮ ይቀቀልና በአራቱም አቅጣጫ ይረጫል። ቂጣ፣ አነባበሮ ተጋግሮ ይረጫል። በደብረ ዘይት ከተማ ግንቦት ወር መስዋዕት ካልቀረበ አሳዛኝ ግድያዎቸን ይፈፀማል። ለምሳሌ እንደ ነገ ሊጋቡ ያሉትን፣ በትምህርታቸው ሊመረቁ አንድ ቀን የቀራቸውን ብቻ በስኬት ጫፍ ያሉትን በመግደል የሚበቀልበት ወር ስለሆነ አባቴ እጅግ የሚፈራው ወር ነው። ሆኖም ግን አልቀረለትም በግንቦት ወር ላይ ሞተ።

 ከሞተ በኋላ ሬሳው ላይ የጉዞ ፍትሀት የሚባል ነገር አለ ሲደገም የሚታደር። ያ ድግምት ደግሞ "ልጆቹ ትምህርት አይማሩ፣  ተበታትነው ይቅሩ፣ ሚስቱ ካለ ባል ትቅር ሰባት ድረስ ቆጥረህ ትውልዳቸውን ተበቀል" ነው እያሉ ቄሶቹ የሚደግሙት። እኛ ቤት ስንክ ሳር የሚባል መፅሀፍ አለ። እዚያ መፅሀፍ ውስጥ ያለው ሁሉ ድግምት ነው። አባቴ ያንን መፅሀፍ በክብር ነበር የሚያስቀምጠው እንደውም አንድ ቀን መፅሀፍ ከተቀመጠበት ምን እንደወሰደው ሳታወቅ ጠፋ "አንቺ ነው የወሰድሽው ይህን መፅሀፍ ካላመጣሽ  እንደከብት ነው የማርድሽ" ብሎ ሲያስፈራራኝ ሳልወስደው " ለሰው ስጥቼዋለሁ አመጣዋለሁ" ብዬ ዋሸሁ። በኋላ ግን ተፈልጎ ተገኘ። ያንን መፅሀፍ ብዙ ቄሶች ይጠቀሙበታል። ያንን የጉዞ ፍትሀት ድግምት ከጨረስኩ በኋላ አባቴ ተቀበረ። ከዚያ በኋላ አባቴ እያለ እቤታችን የሚመጣው ሰው ሁሉ እሱ ከሞተ ዋላ ሁሉም መምጣት ተወ፣ ቤታችን ባዶ ሆነ፣ የምንበላው አጣን። በዚያ ላይ እናታችን ሽባ ሆና አልጋ ላይ ወደቀች። የሞት መንፈስ እየመጣ ያስፈራራታል፣ እኔም ጨካኝ ሰው እያሆንኩ መጣሁ። በግ ሲታረድ ግንባራችንና መሀል እጃችንን ደም እንቀባ ነበርና እኔ አሁን ያ ደም አይደለም ያስደሰተኝ የሰው ደም ነበር የምናፍቀውና አንድ ቀን ለምን እናቴን አልገድላትም ብዬ ቁጭ ብዬ በመጥረቢያ እንዴት አድርጌ እንደምገድላት አስብ ነበር። መንፈሱ የመጨረሻ ጨካኝ ሰው አደረኝ። ከባድ ስራዎችን እሰራለሁ በዚያው መጠን ምግብ አልበላም። የምግብ ፍላጎት አልነበረኝም። አንድም ምግብ መብላት የጠላሁት ተመልሶ ስለሚወጣ ነው። ስጋ ግን በጣም እወዳለሁ ይህ ከመንፈሱ ጋር ትስስር ነበረው። እቤት ውስጥ ስጋ ከጠፋ እናለቅስ ነበር። ዙሪያ ገባችን ጨለመ። ውስጤ በክፋት እየተሞላ በሰላምና በፍቅር የሚያናግሩኝን ሁሉ እንዴት አድርጌ ብገድላቸው እንደምረካ አስብ ነበር። በተለይ ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ ይቀርቡኛል። እኔ ደግሞ እንደነሱ የምላው የለምና በእነርሱ ብዙ እቸገር ነበር። ችግሩ እየፀና ሲሄድና መኖር ሲያቅተን ቤታችንን ማከራየት ጀመርን።

 ለመጀመሪያ ጊዜ ቤታችንን ለመከራየት የመጣችው ክርስቲያን ነበረች። ለመከራየት የመረጠችው ደግሞ የአባቴ መኝታ ክፍል ሰፊ ስለነበር እሱን ነበር። ደብረዘይት ደግሞ ቤት እርካሽ ነውና ዋጋውን ስትጠይቀኝ "መቶ ብር" አልኳት እሷ ደግሞ "ሰማኒያ ብር ልከራይ" ስትል "በፍፁም" አልኳት። ምክንያቱም ጴንጤ ነቻ። ለማንኛውም ነገ እመጣለሁ አለችና በነጋታው ጠዋት ቡና እያፈላን ደረሰች። በመምጣቷ ውስጤ ቢቆጣም ስታዋራኝ ደግሞ ለምን እንደሆነ አላውቅም አሳዘነችኝ። ቤቱንም እንድትከራይ ፈቀድኩላትና ተከራየች። በጣም ጥሩ ሴት ነበረች። እኛ ከመኝታችን ተነስተን እያወራን በራችን ስለተዘጋ ብቻ ተኝተው ይሆናል ብላ ጫማዋን ኮቴ ሳታሰማ ተጠንቅቃ ነው ወደ ክፍሏ የምትገባው። የሚገርመው ደግሞ ሳምንት አስራ አምስት ቀን ትጠፋለች። ከዚያ "ይቺ ሴትዮ ተሰለበች እንዴ? እረ ፖሊስ ጣቢያ እናመልክት" ስንል በሯን ከፍታ ትወጣለች። ለካ ፆም ፀሎት ይዛ ነው። ልክ ስትወጣ በላይዋ ላይ ካለው የእግዚአብሔር ክብር የተነሳ እንኳን ፊቷን ቀና ብሎ ማየት መቆም አንችልም ያንገዳግደናል። ለካ ቀስ እያለች እህቴን እዛ ውስጥ ነክራታለች። ከዚህ በፊት ደግሞ የተነገረን ነገር አለ " እነዚያ ጵንጤዎች ጋር ከሄዳችሁ አትወጡም" እንባል ስለነበር። ለካ ሲገባኝ የማይወጣው የማይለቁት የፍቅር ጌታ ተገኝቶ ነው። እርሱም የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር!

 ከዚያ እህቴ ጌታን መቀበሏን ስሰማ በጣም ተናደድኩ ሁልጊዜ ከእርሷ ጋር መጣላት ሆነ። ከበፊትም ጀምሮ እርስ በእርሳችን መጣላት ከጀመርን ሁሉም ወደ ሆራ ወንዝ ለመግባት እሩጫ ይጀመራል። በኋላ ሰዎች ይዘውን ካረጋጉን በሁዋላ ወደቤታችን ይመልሱናል። በእንዲህ አይነት ሁኔታ ብዙ ጊዜ እየተጣላን ቆየን። ለካ እኔ ሳላውቅ ይቺ ክርስቲያን ተከራያችን እናቴን መስክራላት ጌታን እንድትቀበል አድርጋለች። አንድ ቀን እቤቷ አስገብታ ብዙ ሰዓት እያለቀሰች ትፀልይላታለች።  ከጨረሱ በኋላ እናቴ ቤት ስትገባ በጣም ተቆጣኋት "እንዴት ማርያምን ክደሽ እዚያ ትገቢያለሽ?" አልኳት እሷ ግን እየባሰባት መጣ። ሁሉም ሸርተት እያለብኝ መሄድ ጀመረ። ከዚያ ግቢያችን መስዋዕት አጣ። ለምን እንደሆነ አላውቅም እኔም አባቴ መስዋዕት ያደርግባቸው የነበሩት እቃዎች ሁሉ አውጥቼ መሰባበር ጀመርኩ። ወዲያው ለመቀመጫ የምንጠቀምበት ከባህር ዳር የተገዛ የበግ ቆዳ ብድግ ብሎ መንጓጓት ጀመረ። ግቢ ውስጥ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ጩኸት ያናውጠን ነበር። በዚህ ሁሉ ውስጥ ይህቺ ክርስቲያን እህት ያለመናወጥ ትፀልይልን ነበር። ከዚያ አንድ ክርስቲያን ወንድም ደግሞ ያንን የሚመለክበትን ቤት መከራየት እፈልጋለሁ ብሎ ተከራየ። በቃ ግቢ በሙሉ በክርስቲያን ተወረሰ። እነሱ አንድ ላይ ተሰብስበው ይፀልያሉ። አንዱ ክርስቲያን መዝሙር በደንብ ይከፍታልና አንዳንድ ጊዜ እቃ እያጠብኩ የሊሊንና የምህረት መዝሙር ስሰማ ውስጥን የሚኮረኩር ነገር አለው። ቀስ እያለ መዝሙር  ውስጤ ሲገባ ሳላውቅ አብሬ መዘመር እጀምረና በኋላ እያዘመርኩ መሆኔ ሲገባኝ "ቱ...ቱ... በስመአብ! እንዴ ምን ሆኜ ነው? አሰመጡኝ እንዴ?" እላለሁ።

 መጨረሻ ላይ እናቴም መታመሟ እየፀና ሲመጣ ሁሉ ነገር እንዳልነበረ ሲሆን "የልጆቹ አእምሮ እንዳይጎዳ" ብላ አክስታችን አዲስ አበባ ይዛን መጣች። ይህ ደግሞ ጭራሽ ከእሳት ወደ ረመጥ ሆነ። አክስታችን ሙስሊም ናት ባሏ አረብ ነው። በቃ ያለን እድል "ወላሂ" እያሉ ተደባልቆ መኖር ነበር። የቤቱን ስራ ሁሉ የምሰራው እኔ ነኝ ግን አክስቴ የምሰራው ስራ ሁሉ አያስደስታትም። ልብስ አጥቤ አስጥቼ እንደገና አውርዳ ድጋሚ ታሳጥበኛለች። በዚህ ላይ "ዠንቦ ጠለል" የሚባል መንፈስ ታመልካለች የስሙ አስቀያሚነት በዚያ ላይ መንፈሱ ከበር ውጪ ነው ቡና የሚያስፈላት። ሎሚ ይጨምቅና ቅጠል ላይ ተደግሞ ግቢው ይረጫል፣ ጠዋት ትነሳና ቡናውን ከቆላች በኋላ መኝታ ቤታችን መጥታ የቡናውን ጭስ ታሸተናለች፣ ግቢ ውስጥ በግ እስከ ነፍሱ ትቀበራለች። እንዲህ እየኖርኩ የመጀመሪያ ልጇ ባላሰብኩት ሁኔታ ሊደፍረኝ ሞከረ። ይህን ነገር አክስቴ ስትሰማ "ልጄማ እንዲህ አያደርግም" አለች። ከዚያ ስወጣ ስገባ ትሰድበኝ ጀመር በዚህ ምክንያት ከእርሷ ቤት ወጥተን ቤት ተከራየን እናቴም ከደብረዘይት መጣች። ተከራይተን እየኖርን እያለ የተንደላቀቀ ኑሮ ባንኖርም ደስተኞች ነበርን። አይተነው የማናውቀው ሰላም በቤታችን  ነበር። የሚባላ ነገር እንኳ ባይኖር ስቀን ተጫውተን ያንን ቀን እናሳልፋለን።  ከዚያ ቤት ያከራዩን ሰውዬ  ሌሊት ሌሊት አመድ ላይ ይንከባልላሉ ሲባል እህቴ ሰምታ ነበርና በጣም ነው የምትፈራቸው። እኔ ምግብ ስለምሰራላቸው በጣም ይወዱኛል። በኋላ አንድ ቀን እህቴ አባባ ስምዎት ማን ይባላል? ስትላቸው "ሳይቆረጣጥም ሳይገነጣጥል ዋጥ የሚያደርግ" ሲሏት ተጯጩኸን ወደ ቤታችን ገባን።

 ከዚያን ወዲህ ስለፈራናቸው ሌላ ቤት ተከራይተን ገባን። እዚያ ስንኖር ሰው አይጠጋንም። ለምን እንደሚርቀን አናውቅም። ከዚያ ቤት አከራያችን አንድ ደብተራ ቤት ሄዳ መድሀኒት አሰርታ መጣች። የሚጠጣ ነገር ነውና እንኳን ሊጠጣ ቀርቶ ሽታው በሩቁ ነው የሚያባርረው። ለትምህርትና ወንዶች እንዳይተናኮሉ የሚያደርግ ነው ብላ ሰጠችን። እሱን ጠዋት ጠዋት በባዶ ሆዳችን መጠጣት ጀመርን። እንኳን በትምህርታችን ጎበዝ ልንሆን ቀርቶ ጭራሽ ፈዘዝን። ቤቱ ስላልተመቸን እዚያው አካባቢ ሌላ ቤት አገኘን እና ገባን። አከራዩ ልጅ ክርስቲያን ስለሆነ በጣም ያስጠላኝ ነበር። እርሱ ግን ስለ እኛ ይፀልያል። ከዚያ አንድ ቀን ከቤተሰብ ጋር ድብልቅልቅ ያለ ጠብ ስንጣላ ምን መፅሀፍ ቅዱስ ይዤ ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን ገባሁ። መዝሙር ሲዘምሩ ሰማሁ ጌታን የምትቀበሉ ሲባል ወጣሁና ጌታን ተቀበልኩ፣ ደህንነት ትምህርት ተማርኩ። የጥምቀት ትምህርት ጨርሼ ከተጠመኩ በኋላ የአገልግሎት ትምህርት ሊጀምሩልኝ ሲሉ ፋሁ። በኋላ ባብቲስት ቤተክርስቲያን እያሄድኩ መከታተል ጀመርኩ። እዚያ በውስጤ አጋንንቱ ጮኸ ግን ወጣሁ እያለ ተመልሶ ይገባል። በግራ አውራ ጣቴ መዳፍ ላይ መንፈሱን የሚያስለኝ ቅርፅ ነበር። እንዲሁም የመናፍስቶቹን ስም ዝርዝር ፅፌ ማለትም ጠቋር፣ አዳልሞቴ፣ ብር አለንጋ፣ ሺህ አንበሶ፣ ሞሚና፣ ወሰንጋላ፣ የራያው ጋላ፣ አብዶዬ፣ ወሎ መጀን እነዚህን ከፃፍኩ በኋላ ፈርሜ ግራ እጄን ጨብጬ ለብዙ ጊዜ ማንም አላየብኝም ነበር። አንድ ቀን ግን ቀጠና ሁለት ሙሉ ወንጌል ቤ/ክ ወንጌላዊ መድህን ሲፀልይ "ለብዙ ጊዜ የተቀመጠ አጋንንት ዛሬ ይወጣል" ሲል ከጉባኤው ለመውጣት ስሞክር አልቻልኩም። በኋላ እየተገሰፀ ሲፀለይ ያለሁበትን ቦታ አላውቅም። ብዙ ከፀለዩልኝ በኋላ አጋንንቱ ለቆኝ ሄደ።

 በደንብ ተከታተሉኝ የደህንነት ትምህርት በድጋሚ ተማርኩኝ። ከዚያ ገብቶኝ ጌታን መከተል ጀመርኩ። ይህንን አይቶ ጠላት መፎከር ጀመረ። ጎረቤቶቻችን ሁሉ ጠንቋዮች ናቸው። እንደውም መፍትሄ እናገኛለን ብለው አንድ ጎረቤታችን አሉ ራስታ ናቸው ታዋቂ የሚባሉ ኮሜዲያን፣ ሀብታሞች፣ ጋዴዎች እሳቸው ጋር ይመጣሉና ጠላት በተለያየ መንገድ ይዋጋን ጀመር። አንድ ቀን ቤተሰቦቼ በሙሉ እኔም ጭምር ነስር በነስር ሆንን። የጠላት ውጊያ መሆኑ ስለገባኝ ተነስቼ እያተቃወምኩ "የማንኛችንንም ደም ጠላት አይቀምስም። በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ተሸፍነናል።"" እያልኩ ስፀልይ ወዲያው የሁላችንም ነስር ደረቀ። በጎረቤቶቻችን ላይ የሚሰራውን የጥንቆላ መንፈስ እየተቃወምኩ መፀለይ ጀመርኩ። ከዚያ አንድ ቀን የሰፈራችን ዋና ጠንቋይ የተባለው ሰውዬ ሞተ። የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ እንዳለ ስለተረዳሁ ጠላት በተዋጋኝ መጠን የእኔም ህይወት እየበረታ መጣ።

 ቀድሞ ያንከራተታትን አጋንንት እሷ ደግሞ በተራዋ ቁም ስቅሉን ማሳየት ጀምራለች። ውስጧ የበቀል መንፈስ አለ። በፍቅር ባሸነፋት እግዚአብሔር በመተማመን የገባበት እየገባች ስራውን እያፈረሰች ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞት ወደ ሲኦል ወርዶ ሽንፈቱን በግልጥ እንዳሳየው በጌታ ባገኘችው ድል ብርቱ ሰልፈኛ ሆናለች ነገር ግን ጠላት በውስጧ የሰወረው ደዌ ነበር እሷውው ትቀጥልልን።

 "ከልጅነቴ ጀምሮ የጨጓራ በሽታ ነበረብኝና የተለያየ ሆስፒታል ሄጃለሁ ግን ምንም መፍትሄ አልነበረም። በዚያ ላይ ምግብ ሆዴ ውስጥ አይረጋልኝም። የተለያየ መድሀኒት ይሰጡኛል እወስዳለሁ ነገር ግን ምንም ለውጥ አልነበረም። ህመሙ እየጠናብኝ ሲመጣ ሆስፒታል ሄጄ ስመረመር "ይህ የጨጓራ በሽታሽ ወደ አልሰርነት ተለውጧል" አሉኝ።  በጣም የሚያሰቃይ በሽታ ነው። ጨጓራዬ ላይ ትላትሎች ስለተፈጠሩ ወደ መሳሳትና ወደ መበሳት ደረጃ ደርሶ ነበርና መድሀኒት ሰጡኝ ግን ጭራሽ ባሰብኝ። በኋላ በጌሴም ጋዜጣ ላይ ትንሿ እሳት በኮልፌ የሚል ርዕስ በኮልፌ ቃለ ህይወት ቤ/ክ ስለሚገለጠው የእግዚአብሔር ጣት አነበብኩና በምልክት ወደዚያ ሄድኩ። ህመሙ ፀንቶብኛል፣ ሆዴን በእጄ ደግፌ ነው የሄድኩት። ከዚያ ሰው ሲዘምርና ሲፀልይ እኔ ድምፄን ማውጣት ስለማልችል ዝም ብዬ ነበር የማለቅሰው። በውስጤ ግን "ጌታ ሆይ እባክህ ቢያንስ መፀለይ እንኳን እንድችል እርዳኝ" ስል አገልጋዩ "የጌታ መንፈስ እንደዌቭ ሲንቀሳቀስ አየዋለሁ" ሲል የሆነ ነገር ተሰማኝ። ከዚያ ጨጓራና አስም የሚያማችሁ ወደ መድረክ ኑ ሲባል ወጣሁ። ለሁለችንም ፌስታል ተሰጠን ከዚያ መጋቢ መስፍን የአስም የጨጓራ ህመም በጌታ ኢየሱስ ስም ውጣ ብሎ ሲያዝ ሁሉም ማስመለስ ሲጀምር እኔ ጭልምልም አለብኝ። ከዚያ አገልጋዩ ወደ እኔ ዞር ብሎ " የዘር ማንዘር መንፈስ" እያለ እየተቃወመ ሲፀልይ የበላሁት ነገር አልነበረም ከሆዴ የሆነ ነጭ ነገር ከወጣ በኋላ ውስጤ ነፃ ሲሆን ታወቀኝ። ብዙ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ሲነካኝ እንባ ነው የሚቀድመኝና ውስጤን ፈንቅሎ የሚወጣ ደስታ ነው የተሰማኝ። በወቅቱ መግለፅ የማልችለው አይነት የነፃነት ስሜት ነው የተሰማኝ።"

 አሁንም እንባ አቀረረች። ከዚህ ሁሉ ስለታደገሽ ጌታ ምን ትያለሽ አልናት የምንለው አጥተን ለእኛም የበዛልንን የጌታን ምህረት እያሰብን። "እኔ ስለ ጌታ ለመናገር ቃላት ያጥረኛል። መውጣት ከማልችልበት ሁኔታ፣ ከአጋንንት ወጥመድ ሲያወጣኝ፣ ሀኪም ያልቻለውን መድሀኒት ያላዳነውን ጌታ ግን አልፎ እኔን ማዳኑ ያስደንቀኛል። ጴጥሮስ ስለ ጌታ ለመናገር ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት "ጌታ እኮ ነው" አለ። እኔም ይኸው ነው ቃሌ።

 እንደው በመጨረሻ ልትናገሪ የምትወጂው ነገር ይኖር ይሆን አልናት መለያየታችን እየከበደን። "በተለያየ በሽታ እየተሰቃዩ ላሉ በተለይ ተስፋ እንደሌላቸው በሀኪም ለተነገረላቸው ሰዎች ያለኝ መልዕክት "ኢየሱስ ያድናል" ነው የምለው። ይህን ያመነ ሰው አይፍገመገምም። መከራ የለም ማለት አይደለም። እንደ ኢዮብም መፈተን የለም ማለት አይደለም ግን በዚያ ፈተና ውስጥ ሁሉ ኢየሱስ ትክክለኛ ፈውስ ነው። ምክንያም የእግዚአብሔር ቃል " ፈውስ የልጆች እንጀራ ነው " ይላል። እንጀራ ቀርቦልን የመብላቱን ችሎታ ካላገኘን መብላት አንችልም። ምግብ ቀርቦልን መብላት እየቻልን "አይ እጄ ይቆሽሻል" የምንል ከሆነ መብላቱ ይቀርብናል። ልክ እንደዚህ እግዚአብር ካለ አለ ነው። የእግዚአብሔር ቃል እይሻርምና። በትክክለኛ መስመር ውስጥ ለተገኘ ሰው እግዚአብሔር ይገኛል። ለሰይጣን እራሳችን ፈቅደን ስፍራ ካልሰጠነው በስተቀር ምንም ስልጣን የለውም። ፈቃድ ለሰጡት ግን ብዙ መከራና ብዙ ውድቀት ያመጣባቸዋል። ከሀብታቸው፣ አለኝ ከሚሉት ነገር አጉድሎ ያላቸውን ነገር ጨርሶ ባዶ አድርጎ ለሲኦል ይገብራቸዋል። ስለዚህ ይህን መፅሄት የሚያነቡ ሁሉ ኢየሱስ  ከመከራ፣ ጭንቀት፣ ከሀጢያት ሁሉ ያድናል እላለሁ።"

ጌታ ይባርክሽ ቤቲ

  ኢሜል፡ gesame@ethionet.et

ፖስታ፡ 5925, አዲስ አበባ, ኢትዮጲያ